ኢምፔሪያል አሜሪካ ከየት ወዴት?

የውይይት መድረክ
11 min readMay 21, 2021

የአሁኗ አሜሪካ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ኃያል ሀገር ከሚባሉት ውስጥ አንዷ ናት፡፡ በአለም ዙሪያ ከ800 በላይ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮችን መመስረቷ እና እስከ 40% የሚሆነውን የዓለም ወታደራዊ ወጪ እንደምትመድብ በማየት የአሜሪካንን ሃያል ሃገርነት መረዳት ይቻላል። አሜሪካ የአለም መሪ የሆነችበት ያለፈው ምእተአመትም ሁለት ታላላቅ የዓለም ጦርነቶችን ያስተናገደ ፤ ታይቶ በማይታወቅ የግጭቶች እና በሰው ልጆች ዕድሜ ውስጥ መጠነ ሰፊ ሥቃይ እና ቀውስ የሚገለጽ፤ ከዛም አልፎ እርስ በርሱ የተጠላለፈ የዓለም አቀፍ ሥርዓት የነበረበት ጊዜ ነበር። አሜሪካ አሁን በአለም ላይ ያላትን ሃያልነት ለመረዳት እና አሁን ባለው የዓለም አቀፍ ፖለቲካ የምትይዘውን ቦታ ለመረዳት አሜሪካ ስትመሰረት የነበራትን የአለም አቀፍ ግንኙነት መመልከት ተገቢ ነው።

አሜሪካ መጀመሪያ የነበራት የጋራ ህብረት ከአንድ ሃገር ጋር ብቻ ነበር፤ ከፈረንሳይ ጋር። አሜሪካ በ1776 ብሪታንያን ለማሸነፍ በተካሄደው የአብዮታዊ ጦርነት ከፈረንሳይ ጋር ህብረት መስርታለች። ነገር ግን አሜሪካ በ 1776 ጦርነቱን ካሸነፈች በኋላ ከዓለም አቀፍ ጉዳዮች እና ህብረት ሙሉ በሙሉ ወጥታ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ያ የሆነበት ምክንያት በዚያን ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ከሌላ ሀገር ጋር መተባበር የሚያስፈልገው ለአንድ ዓላማ ብቻ ስለነበር ነው። በዚያን ወቅት አጋሮች በዋነኝነት ጥቅም ላይ የሚውሉት ከሌላ ሃገር ጋር የተወሰኑ ጦርነቶችን ለመዋጋት እና ለማሸነፍ ብቻ ነበር፡፡ አሜሪካ ቀድሞውኑ በሁለት ግዙፍ ውቅያኖሶች (አትላንቲክ እና ፓሲፊክ) ስለምትጠበቅ ከሌላ ሃገር ጋር ልታደርገው የምትችለው ምንም አይነት ጦርነት አልነበረም፡፡ ስለዚህ አሜሪካ ብሪታንያን ካሸነፈች ጀምሮ ለሚቀጥሉት 150 ዓመታት ከአለም ተገልላ እና ተነጥላ የኖረች ብቸኛ ሃገር ነበረች ማለት ይቻላል። እናም በሰሜን አሜሪካ በሁሉም ግዛቶች ተስፋፋች ፣ በመጨረሻም ወደ ምእራብ አቅጣጫ ፓስፊክ ውቅያኖስ በማስፋፋት የአከባቢው ተወላጆች (ኔቲቭ ተወላጆችን) በጅምላ በመጨፍጨፍ አህጉሩን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ቻለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እ.ኤ.አ በ1859 አ.ም ፔንሲልቬንያ የተባለ ግዛት ውስጥ የነዳጅ ዘይት ተገኘ። በወቅቱ የድንጋይ ከሰል ለኢንዱስትሪ ነዳጅ ፍጆታ ይውል የነበረ ቢሆንም ነዳጅ ዘይት እንደተገኘ ዘይትን ፍለጋ ሩጫ (ብላክ ጎልድ ረሽ) ተጀመረ፡፡ ቲቶቪል እና ሌሎች የነዳጅ ዘይት ክሪክ በመባል ሚታወቁ ዳርቻዎች ያሉ ከተሞች የነዳጅ ዘይት ጉድጓዶች እና የማጣሪያ ፋብሪካዎች በመላው የአሜሪካ ግዛች እየተከፈቱ በፍጥነት ተስፋፉ ፡፡ ነዳጅ ዘይት በአሜሪካ ውስጥ በጣም ውድ ዋጋ ካላቸው ዕቃዎች ውስጥም አንዱ ሆነ እና የባቡር ሀዲዶች ወደ ምዕራብ ፔንሲልቬንያ እየተስፋፉ ነዳጅ ዘይት ወደ ቀሪው የአገሪቱ ክፍል መላክ ተጀመረ። የመጀመሪያው የአሜሪካ የነዳጅ ማጣሪያም በ1861 በዘይት ማስተላለፊያ ቱቦ መስመር የሚተላለፍ ሆነ። በወቅቱም አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጣራ ነዳጅ ወደ ብሪታንያ ልካለች፡፡ በመጪው ምዕተ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥም ነዳጅ ዘይት የድንጋይ ከሰልን በመተካት የአሜሪካ ዋነኛ የኢንዱስትሪ ነዳጅ ምንጭ ሆኖ በመቅረቡ ዋና የኢኮኖሚ ሀይል ሆኖ እንዲወጣ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

በ1861 እና 1865 መካከል አሜሪካውያን የእርስ በእርስ ጦርነት ተዋግተው ጦርነቱ ካለቀ በኋላ አሜሪካ ከፓስፊክ እና ከአትላንቲክ ውቅያኖሶች አልፋ መስፋፋት አለባት ወይንስ የለባትም የሚል ክርክር ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ የመጡት እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴዋርድ ያሉ መሪዎች አሜሪካ ዓለም አቀፋዊ ኃይል እንድትሆን ግፊት ማድረግ አለባት ብለው ሲሞግቱ ይህ በተለይ ከእርስ በእርስ ጦርነቱ (1865) በኋላ ትልቅ ክርክር ሆነ፡፡ ሴዋርድ በ 1867 አላስካን ከሩሲያ ለመግዛት ያቀረበውን ሃሳብ በመግፋት ስኬታማ ቢሆንም ግሪንላንድ እና አይስላንድን እንዲሁም በካሪቢያን ውስጥ የተጠቃለሉ ሌሎች አካባቢዎችን ለመግዛት ያደረገው ሙከራ ሁሉም በኮንግረሱ ታግደዋል፡፡ ምክንያቱም ኮንግረስ ውስጥ ብዙዎች ጠንካራ ፀረ-ኢምፔሪያሊስት አቋም ስለነበራቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች አሜሪካ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ የበለጠ እንድትሳተፍ እንዲሁም “ምርጥ ዘር ናቸው” የሚባሉት ነጮች ከ ሌሎች “አናሳ ዘሮች” ጋር መቀላልቀል የለባቸውም የሚል እምነት ስለነበራቸው ነው፡፡ እናም ይህ ተቃውሞ የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊስት ፍላጎት ለመግታት አስተዋጾ አድርጓል፡፡ ነገር ግን በ1800 ዎቹ መገባደጃ ላይ ስለ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ክርክር የሚቀይር አንድ ነገር ነበር፡፡

በ1870 ዎቹ አጋማሽ ላይ የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪ በጥሩ ሁኔታ የተቋቋመ ሲሆን በአሜሪካ ውስጥ የነዳጅ ዘይት ጉድጓዶችን ለመቆፈር እና ምርትን ለመቆጣጠር “መጣደፉ” ተጠናቅቋል፡፡ በፔንሲልቬንያ የነዳጅ ዘይት ምርት በ1891 ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሲሆን በኋላም እንደ ቴክሳስ እና ካሊፎርኒያ ባሉ ምዕራባዊ ግዛቶች ተስፋፍቶ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል። የኢንዱስትሪው አብዮትም እንዲሁ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ያስገኘ ሲሆን እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚ ለማስተዳደር ሲባል ይበልጥ የተማከለ መንግሥት እና ቢሮክራሲን ይፈልጋል በሚል የመንግስት ስልጣን እና ኃይል በፌዴራል መንግሥት እጅ እንዲገባ እና ጠንካራ መንግስት እንዲፈጠር ምክኛት ሆነ፣ እንደ ዊሊያም ማኪንሌይ ያሉ የኢምፐሪያሊስት ሃሳብ ያለቸው ፕሬዚዳንቶች ደግሞ በራሳቸው መንገድ የአሜርካንን ከድንበሯ ውጭ መስፋፋትን አስተባብረዋል፡፡ ማኪንሊ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥመውም አሜሪካ ከስፔን ኢምፓየር ጋር በኩባ ደሴት ላይ ጦርነት እንድትገባ በማድረግ የአሜሪካ ግዛት መስፋፋትን ጉዞ ሀ ብሎ ጀመሯል፡፡

አሜሪካ እ.ኤ.አ. (1898) ፖርቶ ሪኮን ፣ ጉአምን እና ፊሊፒንስን በመጠቅለል የስፔንን ግዛቶች በቀላሉ ወሰደች፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት አሜሪካ የሃዋይ ግዛትን (1898) ፣ የዋቄ ደሴትን (1899) እና አሜሪካዊ ሳሞአ (1900)ን ጠቀለለች፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላም የፓናማ ቦይ አካባቢን (1903) ተቆጣጠረች እና ዶሚኒካን ሪፐብሊክን ለመያዝ በ1916 ወታደሮችን ላከች፤ እንዲሁም የአሜሪካን ቨርጂን ደሴቶችንም ገዛች (1917)፡፡ ይህ የተራራቁ ግዛቶችን በፍጥነት የመጠቅለል ጊዜ አሜሪካን ከጠረፍዋ ውጭ በአለም ካርታ ላይ አስቀመጣት፡፡ በዚህ ወቅትም እያደገ የመጣውን የባህር ንግድ መስመሮችን እና ወታደራዊ ፍላጎቶቿን ለመጠበቅ በሚል እንደ ኒካራጓ ባሉ ቦታዎች ላይ የአሜሪካ ደጋፊ የሆኑ ስርዓቶችን እና ተላላኪ መንግስታትን በመትከል ፤ በእጅ አዙር አሻንጉሊት መንግስታትን በማስቀመጥ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ ዋናውን ሚና መጫወት ጀመረች፡፡

በሌላ በኩል በዚህ የአሜሪካን ተስፋፊነት በተጠናከረበት የመጀመሪያዎቹ አመታት ከአሜሪካ ጋር ተመጣጣኝ የግዛት ስፋት የነበረው የሩሲያ ኤምፓየር ሲሆን በወቅቱ በዛሮች ወይም በፊውዳል ነገሥታት ሲተዳደር የነበረ ሲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ከ1600 ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በግምት 300 ዓመታት ያህል የገዛው የሮማኖቭ ሥርወ መንግሥት አካል ነበር፡፡ በ1900 ዎቹ መጀመሪያ እና በዳግማዊ ኒኮላስ አገዛዝ ወቅትም የአሜሪካ ኢምፔሪያሊስት መስፋፋት እየተጠናከረ ሲመጣ በሩሲያ የገዥው መደብ እና እራሳቸውን የሰራተኛ መደብ (ፕሮሊቴሪያት) ብለው በሚጠሩ መካከል ውጥረት ተፈጠረ፡፡ ፕሮሊቴሪያት በጥንቷ ሮም ውስጥ ድሆችና መሬት የሌላቸውን ፤ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በጣም ዝቅተኛውን ወይም ዝቅተኛውን የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መደቦችን የሚያመለክት መጠሪያ ነበር፡፡ በሩሲያ የገዥው መደብ እና ፕሮሊቴሪያት መካከል ውጥረቱ ተባብሶ የሩሲያ ቦልሼቪች አብዮት ፈነዳና እ.ኤ.አ. በ 1917 ንጉሠ ነገሥቱን ከስልጣን እንዲለቁ በማስገደድ ጊዜያዊ መንግሥት ተቋቋመ፡፡ ሆኖም ጊዜያዊው መንግሥት የሩሲያን ኢኮኖሚ ማረጋጋት ባለመቻሉ ሠራተኞች በተለያዩ ከተሞች መደራጀት ጀመሩ ፣ ራሳቸውን ሶቪዬት ብለው የሚጠሩ የሠራተኛ ምክር ቤቶችንም ማቋቋም ጀመሩ፡፡ የሩሲያ የእርስ በእርስ ጦርነት ከ1917 እስከ 1922 የቀጠለ ሲሆን በሂደት ሩሲያ ሶቪዬት ህብረት ተባለች፣ በኋላም ሶቪዬት ህብረት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከአሜሪካ ጋር የምትተባበር ሃገር ትሆናለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊስት መስፋፋትም ቀጠለ። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት (1914–1918) ሲደረግ አሜሪካ በውጭ ሃገራት ላይ የነበራት ተጽዕኖ ምን ያህል እንደነበረ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው የዓለም ጦርነት በተጀመረበት ጊዜ የነዳጅ ዘይት ለዘመናዊ ጦርነት ፣ መርከቦችን ፣ የመሬት ተሽከርካሪዎችን እና አውሮፕላኖችን ለማንቀሳቀስ ወሳኝ ሆኖ ነበር። የኦስትሮ-ሃንጋሪ ኢምፓየር ባላንጣዎቹን ለማጥቃት በወቅቱ አሜሪካ ወደ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ የምትልከውን የነዳጅ ዘይት መስመሮች በመደምሰስ በሁለቱ ሃገራት የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር አድርጎ ነበር፡፡ በ1917 አሜሪካ ወደ አንደኛው የአለም ጦርነት ስትገባ የኦስትሮ-ሃንጋሪ ኢምፓየር እና በወቅቱ አብዛኛውን የመካከለኛው ምስራቅ ግዛት ተቆጣጣሮ የነበረው የኦቶማን ኢምፓየር በትብብር ፈረንሳይ እና ብሪታንያን ይወጉ ነበር። አሜሪካም ከፈረንሳይ እና ብሪታንያ ጋር በመተባበር የነዳጅ አቅርቦቷን ወደ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ መላክ አጠናክራ ነበር።

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት በጦርነቱ ማብቂያ ወሳኝ ሚና የተረጋገጠ ሲሆን በጦርነቱ ኦቶማን ኢምፓየር እና ኦስትሮ-ሃንጋሪ ኢምፓየር ተሸንፈዋል። አዳዲስ ሃገራት ሲፈጠሩ አብዛኛውን የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ጨምሮ የሁለቱን ኢምፓየሮች ግዛትም ፈረንሳይ እና ብሪታንያ ተከፋፍለዋቸዋል። ከፈረንሳይ እና ብሪታኛ የተረፈውን (ሳኡዲ አረቢያን) አሜሪካ በሂደት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስር ይሆናል። የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ዊልሰንም የአንደኛው አለም ጦርነትን ባጠናቀቀው የፓሪስ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ በመገኘት አለማቀፍ ውሎችን አዘጋጅተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን እና ትብብርን ያሳድጋል የተባለውን የሊግ ኦፍ ኔሽን ምስረታም መርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኮንግረስ አሜሪካ የሊግ ኦፍ ኔሽንን እንዳትቀላቀል ወስኖ ነበር፡፡

በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ አሜሪካ በውጭ አገራት ተጨማሪ የዘይት ክምችት በመፈለግ ተጽዕኖዋን ወደ መካከለኛው ምስራቅ አስፋፋች፡፡ ሆኖም እንግሊዝና ፈረንሣይ የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎችን ከመካከለኛው ምስራቅ ግዛቶቻቸው ለማስወጣት በመሞከራቸው የአሜሪካው ኮንግረስ በ 1920 የፌዴራል መሬቶችን ለኢነርጂ ማእድን ፍለጋ ማከራየትን የሚመለከት የማዕድን ኪራይ ሕግ አወጣ፡፡ ሕጉ ማንኛውም የውጭ ሃገር ኩባንያዎች መንግስታቸው ለአሜሪካ ኩባንያዎች ፍቃድ የሚከለከል ከሆነ በተመሳሳይ በአሜሪካን ሃገር የማዕድን ፍለጋ ፍቃድን የሚከለክል ድንጋጌን ያካትታል ፡፡

እንግሊዝ እና የፈረንሳይ የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎችን ከመካከለኛው ምስራቅ የሁለቱ ሃገራት ቅኝ ግዛት ክልሎች ለማገድ ያደረጉትን ሙከራዎች ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት “ክፍት በር” የነዳጅ ዘይት ዲፕሎማሲን ጀመረ። በዚህም መሰረት ሁሉም ኩባንያዎች መነሻቸው ምንም ይሁን ምን በውጭ ሃገራት ተወዳድረው የነዳጅ ዘይት ያሉባቸውን መሬቶች በቅናሽ እንዲወስዱ አስችሏቸዋል፡፡ የአሜሪካ መንግስት በወቅቱ የጀመረው የነዳጅ ዘይት ዲፕሎማሲ ለሁሉም ኩባንያዎች ክፍት ነበር ይባል እንጂ ሰባት የነዳጅ ኩባንያዎች ጥምረት መስርተው ገበያውን ተቆጣጥረውት ነበር። ለኢራቅ ፔትሮሊየም ኩባንያ የፋይናንስ አቅርቦት የሰጡ ሲሆን ኩባንያዎቹ ከቱርክ እስከ ኢራቅ እና ሳዑዲ ዓረቢያ ድረስ በሚዘረጋው አካባቢ ፤ በወቅቱ ከኩዌት ፣ ኢራን እና ግብፅ አካባቢዎች ውጭ ፤ ራሱን የቻለ የነዳጅ ዘይት ለማልማት የሚያስችል ውል ተስማምተዋል።

ይህ ስምምነት ከአንደኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ የተደረገ ሲሆን የ1928 የቀይ መስመር ስምምነት (1928 Red Line Agreement) በሚል ይታወቃል። ስምምነቱ ሰባት ኩባንያዎች (አምስቱ የአሜሪካ ናቸው) አብዛኛውን የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ የነዳጅ ዘይት ምርትን እንዲቆጣጠሩ አድርጓል፡፡ እነዚህ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎችም “Standard Oil Company of New Jersey (Exxon), the Standard Oil Company of New York (Socony Mobil, Exxon), the Standard Oil Company of California (Socal, Chevron), the Texas Oil Company (Texaco), Gulf Oil (Chevron), Anglo-Persian (British Petroleum BP), and Royal Dutch/Shell” ነበሩ።

እነዚህ ኩባንያዎች በመካከለኛው ምስራቅ ነዳጅ ዘይት እንዲያመርቱ የሚያግዛቸው የ1928 ውል (Red Line Agreement) በወጣበት ወቅትም ከፍተኛ የሆነ የስቶክ ማርኬት ውድቀት እና ኪሳራ በመከሰቱ ከ1929 እስከ 1933 በአሜሪካን ሃገር ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ድቀት (great depression) ተከስቶ ነበር። በተመሳሳይ ወቅትም በአረቢያ አካባቢ የነበሩ የተበጣጠሱ ልዩ ልዩ ጎሳዎችን ፣ የከተማ-ግዛቶችን ፣ በአሚሬትስ እና በአብዛኞቹ የአረቢያ ባሕረ-መንግስታት ላይ እየተካሄደ ነበር። በ 1932 ሳኡድ አብዱልአዚዝ የሚባል መሪ ተገኝቶ ሳዑዲ አረቢያ የሚባል ሃገር ተመስርቷል፡፡ በቀጣዩ አመት 1933 የአሜሪካው ነዳጅ ኩባንያ ቼቭሮን ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት ባገኘው ስምምነት እና ፈቃድ መሰረት አራምኮ (Arabian American Oil Company) የተባለ ግዙፍ ኩባንያ ይመሰረታል።

አራምኮ ከተመሰረተ በኋላ ሳኡዲ አረቢያ በአለም ላይ ካሉ ሃገራት ሁሉ የበለጠ የነዳጅ ሃብት ያላት ሃገር ትሆናለች። አሜሪካ በአለም ላይ የምትከተለው የፖለቲካ እንቅስቃሴም እስካሁን ድረስ በመካከለኛው ምስራቅ ካላት የነዳጅ ዘይት ፍላጎት ጋር በጽኑ የተቆራኘ ሆኖ ዘልቋል። በወቅቱ የአሜሪካው ኩባንያ አራምኮ የነዳጅ ዘይትን ከሳኡዲ አረቢያ ወደ አውሮፓ ፤ አሜሪካ እና የተቀረው አለም ክፍል ለማከፋፈል የሚጠቀምባቸው ሶስት መስመሮችን ነበር።

አንደኛው የባህር ላይ የንግድ መርከብ መስመር በቀይ ባህር በኩል ግብጽ/ሱዌዝ ካናልን አልፎ ሜዴትራንያን ባህርን በመርከብ አቋርጦ ወደ አውሮፓ የሚሄደው ዋነኛው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በህንድ ውቅያኖስ የሰሜኑን የንግድ ባሕር መስመር በሁለቱ ኮርያዎች እና ጃፓን በኩል አልፎ በአርክቲክ በኩል ወደ ሰሜን አሜሪካ የሚያልፈው የመርከብ መስመር ነው። ሶስተኛው እና አማራጭ የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ መስመሮችም በመዘርጋት እቅድ ላይ ነበሩ። በፍልስጤም (በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት) ከቀይ ባህር የአቃባ ሰላጤ እስከ ሜዴትራኒያን ባህር የሚዘረጋ ነዳጅ ማስተላለፊያ ትቦ መስመር እና ከሳኡድ አረቢያ በሌባኖስ ቤይሩት እና ዮርዳኖስ በኩል አድርጎ እስከ ሜዴትራኒያን ባህር የሚዘረጉ የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ መስመሮች (Trans-Arabian Pipeline, Tapline) በመገንባት ላይ ነበሩ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1918ቱ አንደኛ የዓለም ጦርነት የተሸነፈው የኦስትሮ-ሃንጋሪ ኢምፓየር ወደ ናዚ ጀርመን ይለወጥና በ1938 ላይ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ይሆናል፡፡ በምሥራቅ እስያ ጃፓን ከናዚ ጀርመን ጋር በመተባበር በሰሜኑ የንግድ ባሕር መስመር ካላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ የተነሳ “የፐርል ወደብ ጥቃት ደረሰ” በሚል አሜሪካ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ዋነኛ ተሳታፊ ትሆናለች። የሁለተኛው አለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበችው ፍልስጤም ከ 1947 እስከ 1949 በተደረገ ጦርነት ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ትላቀቅና በቦታው ይኖሩ የነበሩ ወደ ሰባት መቶ ሺህ ፍልስጤማውያን ከመሬታቸው ይፈናቀላሉ። በፍልስጤማውያን ላይ የተፈጸምው የዘር ማጽዳት ዘመቻም Nakba በመባል የሚታወስ ሲሆን በፍልስጤማውያኑ ቦታ ከሁለተኛው አለም ጦርነት ጋር በተያያዘ ከአውሮፓ የተፈናቀሉ ስደተኞች (ጂዊሽ/አይሁዳውያን እየተባሉ) ፍልስጤም ላይ ይሰፍራሉ ፤ በ1948 እስራኤል የምትባል ሃገር ትፈጠራለች። አሜሪካም በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ነዳጅ ለመቆጣጠር ዋና መስመሮችንም (ሱዌዝ ካናል እና የሰሜን ንግድ መስመር) አማራጭ መስመሮችንም (እስራኤል በተባለችው ግዛት ከቀይ ባህር የአቃባ ሰላጤ እስከ ሜዴትራኒያን ባህር የተዘረጉ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮችን) በቁጥጥሯ ስር አደረገች።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትን ተከትሎም ዓለም ለሶስት ጎራ ተከፈለች ፣ አንደኛው ዓለም (ራሳቸውን ዴሞክራሲያዊ አገሮች ብለው የሚጠሩ እና በአሜሪካ የሚመራውን የምዕራባውያን አገራት ያቀፈ) ፣ ሁለተኛው ዓለም (ራሳቸውን ኮሚኒስት ብለው የጠሩ እና በሶቪዬት ህብረት የሚመራውን የምሥራቅ አገሮችን ያቀፈ) እና ከሁለቱም ጎራ ያልተሰለፉ የሦስተኛው ዓለም (ታዳጊ ሃገራት) ተባሉ። (የሦስተኛው ዓለም ሃገራት ምንም እንኳን ከሁለቱም ጎራ አልተሰለፉም ቢባልም በተለይ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሁለቱ አለም ሃገራት መቆራቆዣ መድረክ ሆነው እስከዛሬ ድረስ ቀጥለዋል)።

አሜሪካ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ኢኮኖሚዋ ያልወደቀው ብቸኛዋ ሀይል በመሆኗ እና የአቶሚክ ቦንብ መሳሪያ የታጠቀች ብቸኛዋ ልእለ ሃያል ሀገር በመሆኗ በወቅቱ የነበራትን ተጽእኖ በመጠቀም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ለራሷ ጥቅም በሚያመቻት መልኩ ለመፍጠር የሚያስችሏትን ውሎች አዋቀረች፡፡ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተጨማሪም 730 ተወካዮች በተገኙበትና በወቅቱ ከነበሩት 44ቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሃገራት የተውጣጡ ልዑካን በብሬተን ዉድስ ስምምነት ላይ በመመርኮዝ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓትን ዘረጋች። የዓለም ባንክ (World Bank) እና የአለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) የተባሉ ተቋማትም ተመሰረቱ። እነዚህ ተቋማትም በተለይ የአሜሪካንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለማስፈጸም እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ሚና ይዘው ዘለቁ።

የአለም ባንክ እና የአይ ኤም ኤፍ መቋቋም ጉዳይ ግን በወቅቱ የዓለም ሁለተኛው ትልቁ ኃይል የነበረው — የሶቪዬት ህብረት — ነገሮችን በተለየ ሁኔታ እንዲመለከት አድርጎታል። ሶቪዬት ህብረት በሁለተኛው አለም ጦርነት ከምዕራባውያን ሀገሮች ጋር የነበረው አጋርነትም ብዙ ሊቆይ አልቻለም፡፡ አሜሪካም የሶቪዬት ህብረትን በምስራቅ አውሮፓ እና በሌሎች አካባቢዎች ነፃ የንግድ ቀጠና ላይ ቀጥተኛ ስጋት የሚደቅን ነው በሚል ፈረጀችው። ይህንን ተከትሎም የቀዝቃዛው ጦርነት በምእራባውያን እና በምስራቁ አለም ሃገራት መካከል ተጀመረ።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካን የፈጠረችው ሌላ ወታደራዊ ተቋም ደግሞ ኔቶ ነው። የሁለተኛው አለም ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ የአውሮፓ ሀገሮች ደካማ ስለነበሩ አንዳንዶቹ የሶቪዬት ወታደሮች ሊወሯቸው እና ኮሚኒዝምን ሊያስፋፉ ይችላሉ በሚል ስጋት አሜሪካ ከሌሎች 11 ሀገሮች ጋር በመሆን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን መሰረተች። የኔቶ ጥምረት ዋነኛ አላማም ሩሲያ የምእራብ አውሮፓ ሃገራትን ከመውረር እንድትታቀብ ለማስጠንቀቅ በሚል ነበር፡፡ የኔቶ ስምምነት ግልጽ ነበር-በአንድ የኔቶ አባል ላይ የተቃጣ ጥቃት በሁሉም አባላት ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት የሚቆጠር በመሆኑ እያንዳንዱ አባል ወደ እርዳታ እንዲመጣ ይጠይቃል፡፡ እውነታው ግን የበለጠ የተወሳሰበ ነበር ፡፡ አሜሪካ እጅግ ብዙ ወታደራዊ ኃይል ነበራት ፣ እነዚህ ሀገሮችም በጭራሽ ደካማዎች ነበሩ፡፡ ያ ማለት ኔቶ በእውነት እነዚህን ሁሉ ሀገሮች ከጥቃት ለመከላከል የሚችለው በአሜሪካ ዋስትና ነበር ማለት ነው ፡፡ በመሆኑም ብዙዎቹ የአውሮፓ ሃገራት አሜሪካ ከሶቪዬት ጥቃት እንድትጠብቃቸው በማሰብ ድንበሮቻቸው ውስጥ የአሜሪካ ወታደራዊ የጦር ካምፖች እንዲመሰረቱ ፈቅደዋል። እነዚህ የአሜሪካን ጦር ሰፈሮች አሁንም ድረስ አሉ።

ከኔቶ ምስርታ በኋላ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስትከተለው የነበረው ስትራቴጂ ቅድመ መከላከል (“containment”) ሲሆን አላማውም ኮሚኒዝም በዓለም ዙሪያ እንዳይስፋፋ ለመከላከል የሚል ነበር። ይህ የአሜሪካ አዲስ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ስትራቴጂም አሜሪካ ሁል ጊዜ በሁሉም ቦታ ተጽዕኖ ማሳደር አለባት የሚል አፈጻጸምን ተከተለ፡፡ በመሆኑም ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲባል የተፈጠረውን ግዙፍ የወታደራዊ ሃይል ከመበተን ይልቅ ይበልጥ ማስፋፋት አስፈላጊ ነው ተባለ። ይህ መሆኑም ሁለት ዋና ዋና ውጤቶች ነበሩት።

አንደኛ ፣ አሜሪካ እንደ ሳውዲ አረቢያ ፣ እስራኤል እና ደቡብ ኮሪያ ካሉ አገራት ጋር የኮሚኒዝምን መስፋፋት ለመከላከል በሚል ሰበብ የተጠናከረ ወዳጅነት እና ህብረት መሰረተች። በሁለተኛ ደረጃ አሜሪካ የሶቪዬትን ተጽዕኖ ለመግታት በሚል ሰበብ ከበርካታ ሃገራት የውስጥ ጉዳዮች ላይ አብዛኛውን ጊዜ በድብቅ ፤ ሃገራቱ ደካማ ከሆኑ ደግሞ ያለማንም ከልካይ በይፋ ጣልቃ መግባት ጀመረች፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅትም አሜሪካ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግጭቶች ውስጥ ጣልቃ በመግባት በአለም አራቱም ማዕዘናት ውስብስብ የሆነ ጥምረት ፣ ግጭቶች እና ግንኙነቶች ውስጥ ተሳታፊ ሆናለች። ለበርካቶች ሞት ስደት እና መፈናቀልም ዋነኛውን ሚና ተጫውታለች። ይሁን እንጂ አሜሪካ የኮሚኒዝምን መስፋፋት ባቀደችው ልክ መግታት አልቻለችም። በ 1948 ሰሜን ኮሪያ የኮሚኒስት ሀገር ሆናለች፡፡ በ 1949 ቻይናም የኮሚኒስት ሃገር ሆነች፡፡ በመሆኑም አሜሪካ ከስድስት ተጨማሪ አገራት ጋር የተናጥል ህብረት ስምምነቶችን ፈረመች ፡፡ በላቲን አሜሪካም ከ 21 አገራት ጋር የጋራ ህብረት ስምምነት ፈርማለች ፡፡ ከ1989 እስከ 1991 የቀዝቃዛው ጦርነት ሲያበቃ የሶቪዬት ህብረት እና በአውሮፓ ውስጥ የነበሩ የኮሚኒስት አጋሮቻቸው ፈረሱ፡፡ የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎም አሜሪካ ብቸኛ ልዕለ ኃያል ሀገር ሆነች። ቶም እየተስፋፋ መጥቶ ተጨማሪ ሃገራትን አካቷል።

ኔቶ በ 1993 የቀድሞ ሶቪዬት አጋሮችን ፖላንድ ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ሀንጋሪን በአባልነት አካቷል፡፡ ከዚያም አልፎ ኔቶ ከአባላቱ ውጭ ባሉ ግጭቶች ጭምር ጣልቃ መግባት ጀመረ፡፡ ኔቶ በ 1999 በኮሶቮ ውስጥ በሚዋጉ የሰርቢያ ኃይሎች ላይ የቦምብ ድብደባ አድርጓል፡፡ ኔቶ በተጨማሪ በ2001 ከ 9/11 በኋላ አሜሪካን አፍጋኒስታንን እንድትወጋ የረዳ ሲሆን በ2003 ደግሞ በኢራቅ ውስጥ የተካሄዱ ጦርነቶችን በከፊል ተሳትፏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስያ ውስጥ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን ለመቃወም በማሰብ ከደቡብ ኮሪያ እና ከጃፓን ጋር ቅርበት ያለው አጋርነት መሰረተች፡፡ የሶቪዬትን ወረራ ለመከላከል በሚል የተመሰረተው ኔቶም የአሜሪካ መሣሪያ ሆኖ የሶቪዬት ስጋት በሌለበት ወቅትም የአውሮፓ አገራት አንድነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ያስችላል በሚል እስካሁን ድረስ ሳይፈርስ ቆየ፡፡ አሜሪካ ለራሷ በሚጠቅማት መልኩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በአለም ባንክ፣ በአይ ኤም ኤፍ እና ኔቶ በኩል የዘረጋችው አለም አቀፋዊ ስርአትም እስከ ዛሬ ድረስ ይሠራል። እነዚህ ተቋማት እና ስርአቶች እንዲፈርሱ የጠየቀ አንድም የአሜሪካ መሪ አልነበረም — ምናልባትም ከዶናልድ ትራምፕ በስተቀር ፡፡

ቻይና በአሁኑ ወቅት በኤሲያ አሜሪካንን ሊቀናቀን የሚችል የኢኮኖሚ እድገት አምጥታለች። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በሁዋላ ቻይና በዓለም ሁለተኛዋ ትልቁ ኢኮኖሚ ሆና ስለወጣች መላውን የኤሲያ አካባቢ የመቆጣጠር አቅም ያለው ወታደራዊ አቅምም ገንብታለች። አሜሪካ ሩሲያ እና ቻይናን የመቆጣጠር አቅም እንደሌላት ለማሳየት ሁለቱም ሃገራት ግንባር ፈጥረው በቅንጅት በመንቀሳቀስ ላይም ናቸው። ቻይና እና ሩሲያ ለአሜሪካ አጋር ሃገራት አሜሪካ ልትጠብቃቸው እንደማትችል ለማሳየት የሚችሉ ስልቶችንም ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ሁለቱም ሃገራት የራሳቸውን አካባቢያዊ ፍላጎቶች ያላቸው ሲሆን አለም አቀፋዊ ፍላጎቶችም አሏቸው።

ሩሲያ በዋናነት የአርክቲክ አካባቢን እና የሰሜኑን የንግድ መስመር መቆጣጠር ከዚህም የሚገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም በበላይነት መቆጣጠር ትፈልጋለች።አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ከመካከለኛው ምስራቅ ነዳጅ ይልቅ በሩሲያ ነዳጅ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑም ትፈልጋለች። የቻይና የረጅም ጊዜ እቅድ የአሜሪካንን ቦታ መተካት ሲሆን የአለም አቀፍ ንግድን እና የባህር ላይ የንግድ መስመሮችን መቆጣጠር የሚያስችላትን ስትራቴጂ እየተከተለች ነው። ቻይና እና ሩሲያ እነዚህን ፍላጎታቸው ለማሳካት የሚከተሉት አካሄድም ይለያያል።

ሩሲያ በመላው አውሮፓ የሳይበር ጥቃቶችን ስትፈጽም ቻይና በደቡብ ቻይና ባህር የሚገኙትን ጠረፎችን ወደ ሰው ሰራሽ ደሴቶች በመቀየር በደሴቶቹ ላይ ወታደራዊ ካምፖችን እየገነባች ነው። ከአካባቢዋ ውጭ የመጀመሪያ የጦር ካምፗንም ፤ የቀይ ባህር እና የመካከለኛው ምስራቅ የንግድ መስመርን ለመቆጣጠር በሚመስል መልኩ፤ ጅቡቲ ላይ አስፍራለች። ቻይና በምእራብ አፍሪካ ጊኒ ላይ ሁለተኛውን የጦር ካምፕ ለመመስረት እቅድ እንዳላትም ይታሰባል። ከዚህ በተጨማሪም ቻይና በዓለም ዙሪያ በደርዘን የሚቆጠሩ አገራትን ከፍተኛ ብድሮችን እየሰጠች በማማለል የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ስታካሂድ ለአካባቢዎቹ ሃገራት ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትም ታረጋግጣለች፡፡ በሁለቱ ሃገራት የተቀናጀ አካሄድም የአሜሪካ ብቸኛ የአለም ልእለ ሃያል ሃገርነት ከመቼውም ጊዜ በባሰ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ምንጮች 1 2 3 4

--

--